የ13 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ተከላ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል

የ13 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ተከላ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሂጦሳ ወረዳ በኢተያ ከተማ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከሚተከሉ 29 ተርባይኖች የ13ቱ ተከላ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራዎች ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ ገለፁ፡፡

ባለሙያው አቶ ይድነቃቸው ደሳለኝ እንደገለፁት የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም 61 በመቶ ደርሷል።

በፕሮጀክቱ ከሚተከሉት 29 የንፋስ ማማዎች ውስጥ የ23ቱ የመሰረት ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን አፈፃፀሙም 80 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል።

16 የንፋስ ማማዎችን ለመትከል የሚያስችሉ ዕቃዎች ከወደብ ተጓጉዘው ሳይት መድረሳቸውንም ነው አቶ ይድነቃቸው የገለፁት።

እንደ ባለሙያው ገለፃ የአንድ የንፋስ ተርባይን ማማ የመሰረት ሥራ ለማከናወን ከሰባት እስከ 12 ቀናት የሚወስድ በመሆኑ ቀሪ የመሰረትና የተከላ ሥራዎችን በቀጣዮቹ ጊዜያት በማጠናቀቅ በታህሳስ ወር 2018 ዓ.ም ኃይል እንዲያመነጭ ለማድረግ በዕቅድ እየተሰራ ነው።

27 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የውስጥ ለውስጥ የጠጠር አስፓልት መንገድ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ይድነቃቸው አፈፃፀሙም 45 በመቶ መድረሱን ጨምረው ገልፀዋል።

100 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እያንዳንዳቸው 3 ነጥብ 465 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው 29 ተርባይኖች አሉት፡፡

ለግንባታው 145 ሚሊዮን ዩሮ በጀት የተያዘለት ሲሆን የፋይናንስ ወጪውም ከዴንማርክ መንግሥት በተገኘ ብድር እና ስጦታ እየተሸፈነ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።

ግንባታውን በዋናነት ሲመንስ ጋሜሳ ሪኒዌብል ኢነርጂ የተባለ ኩባንያ እያከናወነው ሲሆን ዳር አል ሃንዳሳህ ሼር እና ፓርትነር የተሰኘ ኩባንያ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጅነሪንግ ዘርፍ በአጋርነት በማማከር ሥራው ላይ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ሀገሪቱ ከንፋስ የምታገኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ 544 ሜጋ ዋት ያሳድገዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”